ስለ ሀገሬ ሳስብ . . .የቆምንበት መንገድ መዳረሻው የት ነው?


(ዳዊት ወርቁ)

አራት

የቆምንበት መንገድ መዳረሻው የት ነው?

career-path-1024x531

እንደ ፌስቡክና ዩቲዩብ አይነት የኢንተርኔት ማኅበረሰብ መገናኛ ሚዲያዎች ከተፈጠሩ ወዲህ ብዙ ሰዎች እጃቸውን ፈተዋል:: አንደበታቸውን አላቀዋል:: የታፈኑ ድምጾች አርነት ወጥተዋል:: ሰዎች የመሰላቸውን ይጽፋሉ ይናገራሉ:: ይህ በውነት መልካም ነው:: ጥሩ ጅማሮ ነው:: ጽሑሮች እንደ አሸን ይፈላሉ ቪዲዮዎች እንደጉድ ይለቀቃሉ:: ማለፊያ ነው:: ለዘመናት የታፈኑ ድምጾች ናቸውና መሰማትን ይሻሉ:: መነበብን ይጓጓሉ::

ወዲህ ግን ያልተስተዋለ ጉዳይ ያለ መስሎ ይሰማኛል:: የታፈኑት ድምጾች ሲተነፍሱ ውጤታቸው ዋጋ የሚያስከፍል ሆኖ አየዋለሁ:: ፖለቲካን ሃይማኖትና ብሔርን ወሳኝ አዠንዳዎቻቸው አድርገው የሚያነሱት ሰዎች ጉዳያቸውን በግርድፉ እንደወረደ ስለሚያቀርቡት ዕዳው በተደራሲዎቻቸው ላይ ሲጫን አስተውላለሁ:: ይህንንም ለማረጋገጥ በያንዳንዱ ስሜት ያለቅጥ በሚነበብባቸው ብሔር ተኮር ጽሑፎችና እና ቪዶዮዎች ስር የሚሰጡ አስተያየቶችን መመልከት ይበቃል::

አንዷ በስሜት ከመሬት ተነስታ የእገሌ ብሔር እንዲህ እንዲያ ነው ብላ ጥላሸት የቀባችበትን ቪዲዮ በሚሊየን የሚቆጠር ሕዝብ በሚገለገልበት ማኅበራዊ ድረገጾች ላይ ስለለጠፈች ብቻ ጎሳ ከጎሳ ሲተጋተግ አገር ስትታመስ እናያለን::

ለምሳሌ ለዓመታት ቡና የሚጣጡ ነገር ግን የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑት እናቶቻችን እንዲህ ዓይነት ቪዲዮ በጋራ ቢያዩ ለዘመናት በፍቅርና በሰላም የተገነባው ጉርብትናቸው ባጭሩ እንደሚሻክር ለማወቅ ጥበብ አይጠይቅም::

የትኛውም ከብሔርና ቋንቋ ደም ንጹህ ነኝ የሚል ሰው ባንዲት እዚህ ግቢ የማትባል ብሔርተኛ የገዛ ወገኑ እየተንቋሸሸ ሲያይ በልቡ ምን እንደሚያጭርበት መገመት ቀላል ነው:: ጥላቻ። ምናልባት ሳይታወቀው አብሮት የሚሠራውን አሊያም የሚማረውን የዚያች ሴት ብሔር አባል በልጅቷ አይነት ቢመለከት ላንፈርድበት እንችላለን::

ትዝ ይለኛል አንድ ጊዜ በሁለት የተለያየ ጎሳ አባላት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር:: ታዲያ የአንደኛው ብሔር ተወላጅ የሌላኛውን ብሔር ተወላጅ ገደለው ተብሎ በመላው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የገዳዩ ብሔር ተወላጆች ምንም በማያውቁበት ከማያውቁት ኃጢአት ሲሸሹ እንደነበረ::

እርግጥ ነው ሀሳብን ያላንዳች ተጽእኖ መናገር መልካም ነው:: በያንዳንዱ ሰው ደም ውስጥ ፖለቲካ አለ ሃይማኖት አለ የዘር ጉዳይ አለ እውነት ነው:: ችግሩ ግን አንዱን አንዱ ሳይጎዳ ሃሳብን መሰንዘሩ ላይ በመሆኑ ባንድ ግለሰብ ምክንያት ሀገር ሲታመስ እርስ በርስ የጎሪጥ ስንተያይ ከባልሽ ባሌ ይበልጣል ሽሮ አበድሪኝ ስንባባል የቆምንበት መንገድ መዳረሻው ወዴት ነው እንድል እገደዳለሁ::

ማኅበራዊ ሚዲያው በነዚህ ጉዳዮች ላይ ብዙ መስራት ቢጠበቅበትም እንደ ሰብአዊ ሰው ግን ይልቁንም ፊደል እንደቆጠረ ሰዎች በተለይም እግዚሐር እኩል አርጎ የፈጠራቸውን ነገር ግን በቋንቋ ብቻ የሚለያዩትን ሰዎች እየለያዩ ማናቆር ለኔ የሰይጣን ሥራ ይመስለኛል:: ኦሮሞ አማራ ትግሬ ወዘተ . . . ኢትዮጵያ በምትባል ሀገር ለዘመናት ኖረናል:: እየኖርንም ነው:: በብሔርና ቋንቋ ተቧድኖ መተጋተጉ ግን እንግዳ ክስተት ነው:: ይህ ነገር ከባድ ነው:: መጨረሻው ጥፋት ነው::

ከጎረቤቶቻችን ብዙ መማር እንችላለን:: ሩቅ ሳንሄድ የሩዋንዳ ወንድማማቾች የነበሩትን የሁቱና ቱትሲ ጎሳዎችን ማየት እንችላለን:: ሁለቱ ነገዶች ቋንቋና ዘር ባመጣባቸው ዳፋ ምክንያት በሚልየን የሚቆጠሩ ወገኖቻቸው ደመ ከልብ ሆነዋል:: የነሱ ደም ገና አልደረቀም::

በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሆነን ብናወራ ነገድ ነው ብናስብ ጎሳ ነው ብናሰላ ብሔር ነው ብናምጥ ቋንቋ ነው:: የትውውቃችንና የወዳጅነታችን መሠረቱ ፍቅር ሳይሆን ሰውነት ሳይሆን ቋንቋ ነው ብሔር ነው::

አንዱን ብሔር እያጠለሸንና እየረገምን የጀመርነው ጉዞ መጨረሻው የት ነው? . . .

Posted in ጉዳዮች - Affairs, Social Life, The Blogger's Diary | Tagged , , , , | Leave a comment

ስለ ሀገሬ ሳስብ . . . ነቢዩ ናታን ወዴት ነህ?


(ዳዊት ወርቁ)

ሶስት

ነቢዩ ናታን ወዴት ነህ?

632_2

Ethiopian main religions leaders (photo credit Google)

አንድ ጊዜ እንዲህ ሆነ ይባላል:: ንጉሥ ዳዊት በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ላይ “ወክ” ሲበላ ቤርሳበህ የተባለችውን ቆንጆ ሴት ገላዋን ስትታጠብ አየ:: ተመኛትም:: እንደተመኛት አልቀረም ሰው ልኮ እልፍኙ ድረስ አስመጣት:: ተኛትም:: ቤርሳቤህ ጸነሰች::

“ጸንሻለሁ” ስትፈራ ስትቸር ነገረችው::

ንጉሥ ደነገጠ::

የተከበረው ንጉሥ በገዛ ወታደሩ ሚስት ስሙ እንዲጠፋ አልፈለገም::

ዘዴ ቀየሰ::

ኦርዮን የተባለውን የቤርሳቤህ ባል ከጦር ሜዳ አስመጣው:: ኦርዮን መጣና እጅ ነሳ::

“ኦርዮን ጀግናው ወታደሬ እንኳን በደህና ተመለስህ::”

ኦርዮን የንጉሥ ማዕድ ተዘጋጀለት:: ከወይን ጠጁም አንድ ሁለት አለ:: ኦርዮን ሞቅ አለው::

“በል ተነስ ደግሞ ከሚስትህጋ ዓለምህን ቅጭ ” አለው ንጉሡ::

ከንጉሡ የተጸነሰው ጽንስ ከምስኪኑ ኦርዮን ተብሎ እንዲታሰብ ነው:: ንጉሡ ላፍታም ቢሆን እፎይ አለ:: ኦርዮን እጅ ነስቶ ወጣ::

በማግሥቱ ግን ንጉሡ ኦርዮን ከሚስቱጋ እንዳልተኛ ወሬኛ ሹክ አለው:: ንጉሡም ያስጠራውና

“አዳር እንዴት ነበረ?” ይጠይቀዋል

“ጌታዬ መልካም ነበረ”

“ሚስትህን እንደናፈቅሃት አገኘሃት?”

“የለም ጃንሆይ እኔ እበረንዳ ላይ እንጂ ከሚስቴጋ በልፍኝ አልተኛሁም”

“ለምን ቢባል?!”

“ጃንሆይ ጓደኞቼ በጦር ሜዳ ግንባራቸውን ላረር ጀርባቸውን ለጦር እየሰጡ እኔ ከሚስቴጋ መደሰት እንዴት ይሆንልኛል?”

ንጉሡ ዘዴው እንዳልሰራለት ሲያውቅ ተናደደ:: ለሁለተኛ ጊዜ ተመሳሳይ ሙከራ አደረገ:: ሰውየው ግን በጅ የሚል አልሆነም::

ይህን ጊዜም ነው እንግዲህ ንጉሡ በራሱ በኦርዮን የሞቱን ደብዳቤ አሲዞ ወደ ጦር ግንባር የላከው:: ደብዳቤው ለጦር አዛዡ ለኢዮአብ የተጻፈ ሲሆን ባጭር አማርኛ “ይህን ሰው ጦሩ በተፋፋመበት ቦታ አሰልፈው” ነው የሚለው:: የጦር አዛዡ የንጉሡን ትዛዝ ለመፈጸም አፍታም አልፈጀበትም:: ንጉሡ እንዳሰበው የጠላት እርሳስ ከኦርዮን ግንባር ስትቀረቀር አልዘገየችም:: ኦርዮን ሞተ:: ንጉሡ ለሁለተኛ ጊዜ እፎይ!!! . . . አለ::: በቃ ዘዴዬ ሰራልኝ አለ:: በቃ የተረገዘው ልጅ ከኦርዮን እንደሆነ ሕዝቡ ያውቃል አለ:: እውነቱን ነበረ:: DNA የለ ምን የለ::

ንጉሡ እፎይ ብሎ በጀርባው ጧ ብሎ ሳይተኛ ግን ሌላ ዱብ ዕዳ መጣበት::

አሽከር ይመጣና

“ጃንሆይ ነቢዩ ናታን መጥተዋል”

“አስገቡት”

ነቢዩ ናታን መላ ሰውነቱ በቁጣ ፍም ግሎ ከንጉሱ ፊት ቆሟል:: ንጉሡ ባርምሞ እያስተዋለው

“ነቢዩ ናታን ምን እግር ጣለህ?”

“ንጉሥ ሆይ በከተማችን አንድ ሐብታም ሰው ነበረ:: ብዙ በጎች የበዙለት ሰው ነው:: ደግሞ የሱ ተቃራኒ አንድ ደሃ አለ አንድ በግ ብቻ ያለው:: እንደ ልጁ የሚሳሳላት አንድ በግ ብቻ ነው ያለው::”

ንጉሡ በጣም ጓጉቶ “እ . . . ሺ”

“ያ ሐብታም የሺ በጎች ጌታ የዚያን ደሃ አንዲት በግ ነጥቆ አርዶ በላበት::”

“ምን?!!! ይህ ሰው መገደል አለበት!!” አለ ንጉሡ ሲፈርድ ሰከንድ አልፈጀበትም::

ነቢዩ ናታን የተናገረው ግን የጨው ዓምድ አደረገው::

“ንጉሥ ሆይ ያ ሰው አንተ ነህ!!”

ንጉሡ ከሰዎች የደበቀው ደባ ልብንና ኩላሊትን ከሚመረምር ከእግዚአብሔር እንዳልተሰወረ ለመረዳት ጊዜ አልፈጀበትም:: ማቅ ለብሶና በጸጉሩ ላይ አመድ ነስንሶ እያለቀሰ አቤቱ በድዬሃለሁና ማረኝ እያለ ንስሃ ሲገባም አልዘገየም::

ጥያቄዬ የዘመናችን ናታኖች ወዴት ናችሁ? . . . ባለብዙ ሺ በጎቹ መንግሥታችን የአንድ ደሃ በግ ነጥቆ ሲያርድ ለመናገር አፋችሁን ምን ሸበበው? . . . ወደ ገዛ ወገኖቹ አፈሙዙን ሲያዞር ተው እግዚሐርን ፍራ የምትሉ ናታኖች ምን ውስጥ ናችሁ? . . . መቼ ነው አገልግሎታችሁ ከጨጓራና ኩላሊት በሽታ መገለጥ እልፍ የሚለው? . . .

ይቀጥላል . . .

Posted in ጉዳዮች - Affairs | Leave a comment

ስላገሬ ሳስብ . . . ኢሕአዴግና የሃይማኖት ነጻነት


ሁለት

ኢሃዲግና የሃይማኖት ነጻነት

eprdf

EPRDF’s logo (photo credit Google)

በሰሞኑ ሁኔታ ካንዲት ጴንጤ ዘመዴ ጋር እያወራን ነው:: በሰሞኑ ሁኔታ ስል ግልጽ ነው አይደል? . . . በሕዝብና በመንግሥት መካከል ስለተፈጠረው እንካ ሰላንቲያ ማለቴ ነው:: በርግጥም መንግሥትና ሕዝብ ሆድና ጀርባ ከሆኑ ሰነበቱም አይደል እንዴ? . . . (መንግሥታችን ሆይ ባጋጣሚ ይህንን ጽሑፍ የምታነብ ከሆነ ከውስጡ አንዳች ቁምነገር አታጣምና እባክህ አትናቀው)

እናም ዘመዴ

“ኢሃዴግ ክፉ እንዲደርስበት አልፈልግም” አለችኝ

“ምክንያት?” ጠየኳት::

” ምክንያቱማ ኢሃዲግ ባይኖር ኖሮ እግዚአብሔርን ማምለክ አንችልም ነበረ” አለችኝ::

“ምን ማለት ነው?”

“በደርግ ጊዜ ቤተክርስትያን ስደት ላይ ነበረች ዕድሜ ለኢሃዲግ . . .” ብዙ አለች ዘመዴ::

እርግጥ ነው ደርግ ሃይማኖት የለሽ ሥርዓት ነበረ:: ሃይማኖትንም አሳዳጅ ነበረ:: እርግጥ ነው ደርግ ብዙ ለነፍሳቸው ያደሩ ሰዎችን ነፍስ ቀርጥፎ በልቷል:: ብዙዎችን በወህኒ አማቆ ገሏል እውነት ነው::

እርግጥ ነው ኢሃዲግ ደርግን ሲጥል ከደርግ ውድቀት ብዙ ነገር ተምሯል:: ሕዝቡ የደርግን ሥርዓት ከተጸየፈበት ነገር አንዱ ደርግ ሃይማኖት አሳዳጅ ሥርዓት እንደሆነ ልብ ብሏል:: ስለዚህ ፈጣሪ የለም ብሎ ሃይማኖትን ሊያስክድ ቆርጦ የተነሳውን ደርግ ኢሃዴግ ፈጣሪ አለ ብሎ የእምነት ነጻነትን ሰንደቅ እያውለበለበ መጥቶ የሸፈተውን የሕዝብ ልብ አገኘ:: ታላቅ ብልጠት! በውጤቱም ቅጥ ያጣ የሃይማኖት ነጻነት (በተለይም በፕሮስቴንታንቱ ዓለም የማምለኪያ ቤት እዚህም እዚያም እንደ ሱቅ እስኪከፈትና ቢዝነስ እስኪሆን ድረስ) በገፍ ሰጠ::

እርግጥ ነው እንደ ክርስትና ሃይማኖት አይደለም በኢሃዴግ ላይ በጠላትም እንኳ (ጠላት ካለ:: ምክንያቱም እንደ ክርስትና እምነት ጠላታችን ሰይጣን ዲያብሎስ እንጂ ሰዎች አይደሉም) ክፉ እንዲደርስ አስፈላጊ አይደለም:: “ጠላትህ ቢራብ አብላው ቢጠማ አጠጣው” እንዲል ቃሉ:: ይህ ደግሞ የክርስትና ሃይማኖት ሥረ መሰረት ፍቅር እንጂ ጥላቻ ባለመሆኑ ነው::

ወደ ዋናው ስቱዲዮ ስንመለስ . . . የዘመዴ የኢሃዴግን ክፉ አለመመኘት ከዚያ የመነጨ ነው::

እኔን ጨምሮ ብዙ ጴንጤዎች ስለ ኢሃዴግ ስናስብ ወዲያውኑ ትዝ የሚለን የሃይማኖት ነጻነት ጉዳይ ነው:: ኢሃዴግ ባይኖር ኖሮ የሃይማኖት ነጻነታችን ውሃ ይበላው ነበር እንላለን::

ኢሃዴግ ሲመጣ በርግጥም ለሃይማኖታችን ቀን ወጥቶልናል:: ያ ማለት ግን ቀን ያወጣልን አምላካችን ነው እንጂ ኢሃዲግ አይደለም:: በርግጥ ኢሃዲግ መሣሪያ ሆኗል:: ስለዚህ ክሬዲቱ ለምናመልከው አምላክ እንጂ ለኢሃዲግ ፈጽሞ የሚገባው አይደለም እላለሁ:: እንዲያ ማድረግ በራሱ ኅጢያት ይመስለኛልና::

ባንጻሩ ኢሃዲግን ለሃይማኖታቸው ነጻነት ፋና ለኳሽ አድርገው የሚያምኑ የዘመዴ ቢጤ በሚልየን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ:: ከምእመን እስከ የሃይማኖት መሪዎች:: የኢሃዴግ ሥርወ መንግሥት ቢቀየር የሃይማኖታቸው ነጻነት ገደል የሚገባ የሚመስላቸው ብዙ የዋሃን አሉ:: ስለዚህ ኢሃዴግን የተቃወመ እግዚሐርን እንደተቃወመ ነው:: በእርግጥ ምክንያቱ ይህ ብቻ ሳይሆን “ነፍስ ሁሉ ለባለሥልጣኖች ትገዛ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ዋና ምክንያታቸው ነው::

“ነፍሥ ሁሉ ለባለሥልጣኖች ትገዛ::”

ይቀጥላል . . .

Posted in ጉዳዮች - Affairs | Leave a comment